ስለ ምርኩዝ

ምርኩዝ እ.ኤ.አ. በ 2023 በተለያየ የሙያ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ከጤና ባለሙያ እስከ ሥራ ፈጣሪ ድረስ ሰፊ የሙያ ልዩነት ነገር ግን አንድ አይነት ራእይ ባላቸው ግለሰቦች የተቋቋመ ማህበር ሲሆን ዓላማውም ለካንሰር በሽተኞች እንክብካቤ እየሰጡ ላሉ ግለሰቦች እና ቤተሰቦች በመረጃ ላይ የተመሰረተ የህክምና ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ማስተማር ፣ ማበረታታት እና መርዳት ነው። ሁሉም ሰው ልዩ የሆነ አካላዊ፣ ስሜታዊ እና መንፈሳዊ ፍላጎቱን የሚያሟላ ተገቢውን የካንሰር ህክምና እና እንክብካቤ ማግኘት እንዳለበት እናምናለን፡፡ አላማችንም የካንሰር ህሙማን እና ተንከባካቢዎቻቸው በዚሀ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ሲያልፉ አስፈላጊውን እውቀት የሚያገኙበት፣ መረጃ እና ልምድ የሚለዋወጡበት እና እርስ በርስ የሚደጋገፉበት ቤተሰባዊ መድረክ መገንባት ነው።

ታሪካችን

ምርኩዝ እ.ኤ.አ. በ 2023 በተለያየ የሙያ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ከ ጤና ባለሙያ እስከ ሥራ ፈጣሪ ድረስ ሰፊ የሙያ ልዩነት ነገር ግን አንድ አይነት ራእይ ባላቸው ግለሰቦች የተቋቋመ ማህበር ሲሆን ዓላማውም ሰዎችን ለመርዳት ነው። የሁለቱ መስራች አባሎቻችን አባት የሆነው የሸዋሉል ተሰማ በ2022/2014 ነበር ወደ ጉበቱ የተሰራጨ የቆሽት(ጣፍያ) ካንሰር እንዳለበት የታወቀው ። የሚወዱትን ሰው ልክ አብዛኛዎቹ የካንሰር ህሙማን ላይ በሚታየው ፍጥነት እየደክሙ ሲመጡ መመልከት በጣም ከባድ ቢሆንም እንዴት መርዳት እንዳለቦት ካለማወቅ የሚመጣው ተስፋ ቢስነት ጉዳዩን የበለጠ ከባድ ያደርገዋል። የየሸዋሉል ቤተሰቦች የጤና ባለሞያ ከመካከላቸው በመኖሩና የበሽታውን ባህሪ ስለሚያውቁ እና ለሰዓታት የሚፈጅ ጥናት በበኩላቸው ስላደረጉ ብዙም አልተቸገሩም። ይህን ክፍተት ባስተዋሉበት ጊዜ ነበር  በኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ካንሰር እና የካንሰር በሽተኞችን እንዴት መንከባከብ እንደሚቻል የመረጃ እጥረት እንዳለ መገንዘብ የቻሉት::

አላማችን

አላማችን ለካንሰር ህሙማን እንክብካቤ እየሰጡ ላሉ ግለሰቦች እና ቤተሰቦች በመረጃ ላይ የተመሰረተ የህክምና ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ማስተማር እና ማበረታታት ነው። ሁሉም ሰው ልዩ የሆነ አካላዊ እና መንፈሳዊ ፍላጎቱን የሚያሟላ ተገቢውን የህይወት መጨረሻ እንክብካቤ ማግኘት እንዳለበት እናምናለን፡፡ ለዚያም የህይወት ጥራትን ለማሻሻል ስለ የካንሰር ህሙማን የመጨረሻ ቀናት እንክብካቤ ምንነት ፣ እንዴት እንደሚሰራ እና ከእንክብካቤ ስጪው ምን እንደሚጠበቅ ብዙ መረጃ እናቀርባለን፡፡ በገንዘብ ወይም በሌሎች መሰናክሎች ምክንያት የካንሰር ህሙማን የመጨረሻ ቀናት ወይም የሆስፒስ እንክብካቤ ማግኘት ላልቻሉ ግለሰቦች እና ቤተሰቦች ድጋፍ ለመስጠት ቆርጠን ተነስተናል። የመክፈል አቅሙ ምንም ይሁን ምን ሁሉም ሰው ከፍተኛ ጥራት ያለው የካንሰር ህሙማን የመጨረሻ ቀናት/የሆስፒስ እንክብካቤ ማግኘት ይገባዋል ብለን እናምናለን።

የካንሰር ህሙማን የመጨረሻ ቀናት ወይም የሆስፒስ እንክብካቤ ህይወትን በሚገድብ ህመም ውስጥ እንኳን ህይወትን ሙሉ ለሙሉ በምቾት መኖር  ይግባቸዋል ብለን እናምናለን፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ጉዞ ውስጥ ግለሰቦችን እና ቤተሰቦችን ለመደገፍ እና ፍላጎቶቻቸው እና ምኞቶቻቸው እንዲሟላ ለማድረግ እንጥራለን። 

ራዕያችን

የካንሰር ህሙማን እና ተንከባካቢዎቻቸው በአስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ለማለፍ አስፈላጊውን እውቀት የሚያገኙበት ፣ መረጃ እና ልምድ የሚለዋወጡበት እና እርስ በርስ የሚደጋገፉበት ቤተሰባዊ መድረክ መገንባት ነው። እናም የካንሰር ህሙማን የመጨረሻ ቀናት ወይም የሆስፒስ እንክብካቤን የጤና እንክብካቤ መሰረታዊ አካል በማድረግ ታማሚዎች እዲሁም ቤተሰቦቻቸው በመረጃ ላይ የተመሰረተ የህክምና ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ የሚያስፈልገውን ድጋፉ ከማድረግ በተጨማሪ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን እና ርህራሄ ያለው የህይወት መጨረሻ እንክብካቤ እንዲያገኙ ማመቻቸትን አላማ አድርገናል፡፡ ለዚህ ራዕይ ምሳካት እለት ከእለት ለመስራት ቆርጠን ተነስተናል፤ እናም በዚህ አስፈላጊ ተልእኮ ውስጥ ከእኛ ጋር እንዲተባበሩ እንጋብዝዎታለን።

የጤና መረጃ ማቅረብ

በአሁኑ ወቅት ምርኩዝ ከጤና ጋር የተገናኙ መረጃዎችን በዋናነት በተለያዩ የካንሰር አይነቶች እና ቀሪ የህይወት ዘመናቸው ከስድስት ወር በታች ለሆኑ ግለሰቦች የህይወት መጨረሻ እንክብካቤ አሰጣጥ ላይ ያተኮሩ መረጃዎችን  በመስጠት ላይ ይገኛል። ይህ ጠቃሚ የጤና መረጃ በዋነኛነት በድረ-ገፃችን ፣ ዩቲዩብ ቻናላችን ፣ ፌስቡክ ፣ ቲክቶክ ፣ ሊንክደን እና ትዊተር ባሉ ማህበራዊ ሚዲያ/ዲጂታል መድረኮች እያሰራጨን እንገኛልን። ብዙ ተመልካቾችን ለማግኘት እና ተደራሽነታችንን ለማስፋት መረጃዎችን በእነዚህ መድረኮች ለማቅረብ እንተጋለን ።

በጎ አድራጎት

እኛ ምርኩዞች  እያንዳንዱ የካንሰር ታማሚ የመክፈል አቅሙ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን አለ የተባለውን ምርጥ የጤና እንክብካቤ ማግኘት እንዳለበት አጥብቀን እናምናለን። የሕክምና ወጪዎች የፋይናንስ ጫና አዳካሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ስለምንገነዘብ የእርዳታ እጃችንን ለማቅረብ ዝግጁ ነን። ማንም ሰው ካንሰርን በሚዋጋበት ጊዜ ተጨማሪ የገንዘብ ችግር እንዳይገጥመው ለመርዳት እንጥራለን።

የወደፊት እቅዳችን

ስልጠናዎች

ማህበራችን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለካንሰር ታማሚዎች እና አስታማሚዎች ልዩ ስልጠናዎችን ለመስጠት አቅዷል። ይህ ተነሳሽነት የካንሰር በሽተኞችን በመንከባከብ ረገድ ወሳኝ ሚና ለሚጫወቱ ሰዎች ጠቃሚ እውቀት እና ድጋፍ ለመስጠት ያለመ ነው።

ትርጉም ያለው ግንኙነት መፍጠር

በአዲስ ተመራቂ ዶክተሮች እና ነርሶችን በቤታቸው ሆንው የህይወት መጨረሻ ህክምና እና እንክብካቤ እያገኙ ካሉ ታማሚዎች ጋር የሚገናኙብትን መንገድ ለመፍጠር በእቅድ ላይ ነን። ይህ ተነሳሽነት የመጨረሻ የህይወት ደረጃ ላይ ላሉ ታካሚዎች እርዳታ እና የህክምና እውቀትን ለመስጠት ያለመ ነው።

አላማችንን ለመደገፍ እና ለመሳተፍ ምልክቱን ይጫኑ

የእርስዎ አስተዋፅዖ መጠኑ ምንም ያህል ይሁን በሚያስፈልጋቸው የካንሰር ሕሙማን ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።

Scroll to Top